ባንድ ወቅት የሐብታም ቤተሰብ ልጅ ቤታቸው ድረስ እየሄድኩ ከመደበኛ ትምህርቷ ባሻገር በትርፍ ጊዜዋ ሳስጠናት ያጋጠመኝ እንዲህ ነው፡፡
የማስጠናት ልጅ ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ አዲስ አበባ ከተማች ውስጥ በሚገኝ ዝነኛና የሐብታምና ባለሥልጣናት ልጆች ከሚማሩበት ትምሕርት ቤት ውስጥ ትማራለች፣ ወላጆቿ የተረፋቸው ናቸውና፡፡
ልጅቱ በተፈጥሮ የታደለችው ብሩህ አእምሮ ሲኖራት፣ ገና ከጅማሬው የምታስባቸው ነገሮችና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎቷ የሚገርም ነበረ፡፡ ምንም እንኳ ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ብትሆንም ቅሉ፣ አመጋገቧ የተመጣጠነ ስለሆነ ሰውነቷ ያለ እድሜዋ አሳጥቷል:፡፡ ባጭሩ የአስራ ሁለት አመት ልጅ ሆና ሳለ፣ ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ኮረዳ ትመስላለች፡፡ ይሁንና ወንድ ስታይ፣ (እኔ አስጠኚዋን ጨምሮ) አንዳንድ ድንበር የዘለሉ ባህሪያት (ታላላቆቿ እንደሚያደርጉት) ታሳይ ነበርና በጊዜው የነበረው ሁናቴዋ አደጋ ላይ እንዳለ ያመላክታል፡፡
ትዝ ይለኛል በጊዜው ቲቪ አፍሪካ በሚባል ቴሌቪዢን ጣቢያ ላይ “ላቪንግ” የሚል ፊልም ይተላለፍ ስለነበረ ልጅቱ በፊልሙ አለቅጥ ተነድፋ ኖሮ ሱሰኛ ሆናለች፡፡ ታዲያ ያቺ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መላ ነገሯ እየተለወጠ ሲመጣ አስተውላለሁ፡፡ ለምሳሌ ላስጠናት በምሄድበት ሰዓት፣ ኩል ተኩላ፣ በቻፕስቲክ ከናፍሮቿን አውዝታ፣ አገኛታለሁ፤ ይባስ ብላም በማስጠናት ጊዜ በሐሳብ ማዕበል ጭልጥ እያለች፣ ደግሞ ትምህርቱን ይዛው እንደሆነና እንዳልሆነ ስጠይቃት ደርሳ ድንግጥ እያለች፣ ሲላት እየተሽኮረመመች፣ እያፈረች መከራዬን አሳየችኝ፡፡
በወቅቱ ከዚያች አንድ ፍሬ ሕጻን የማይጠበቅ ባሕርይ ነውና ሁናቴዋ እንዲያው ሁሉን ለማወቅ መሻት የመጣ እንጂ ፈጽሞ ሌላ ነገር አልመሰለኝም፡፡ ይሁንና ስለፍቅር እንድተርክላት፣ ስለወንድና ሴት ተፈጥሮ እንዳወራላት፣ ስለ እራሴ ግላዊ ሕይወት እንድዘበዝብላት ግድ ትለኝ ጀመር፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን፣
"Mister, do you know I am the only girl in our class who doesn’t have a boy friend?" ትለኛለች::
"No, I don’t know." እየደነገጥሁ::
"I am the only lonely girl." እንባዋ ባይኗ ግጥም ብሎ ካሁን አሁን እንደ ሐምሌ ዝናብ መጣሁ መጣሁ እያለ፤
What about the rest of the class?
They all have, but me. እንባዋ አሻፈረኝ ብሎ ግድቡን በመጣስ በጉንጮቿ ላይ ኩልል እያለ::
How it could be? አንቺኮ ገና ልጅ ነሽ፣ በዚያ ላይ ገና…
No, don’t say like that Mr. please? አቋረጠችኝ፤
Listen to me Sara (ስሟ ተለውጧል) when you become a big girl, like your older sister, you will have your own boy friend, but this is not the right time. And the only thing that what everybody expecting from you is just focusing on your school.
እንዲያም ሆኖ ምክሬ በጥቁር ድንጋይ ላይ ውሃ እንደ ማፍሰስ ከንቱ ሆኖ ቀረ::
ሲውል ሲያድርም ያቺ ጎበዝ ተማሪ የፈተና ውጤቷ እንደ መንገደኛ ስንቅ እየቀለለ እየቀለለ ሲመጣ አንድ ቀን እናቷን ጠራኋቸውና፣
“ልጅዎ እየደከመችብኝ ነው”
“ምን ማለት ነው?”
“በትምሕርቷ እየወረደች ነው”
“አንተ እያለህ እንዴት ይሆናል? የቀጠርንህ ለእንደዚህ አይነት ችግር መስሎኝ”
“ልክ ነው፤ የእኔ ርዳታ ግን ማስጠናት የቤት ስራዎቿንና አሳይመንቶቿን በጊዜ መስራት አለመስራቷን መቆጣጠርና ማሰራት እንጂ የባህርይ ለውጥ መቆጣጠር አይመስለኝም ”
“ልጃችን ባህሪዋ ተለውጧል እያልክ ነው?”
“አዎ በጣም፡፡ በእሷ እድሜ የማይታዩ ባህሪያት አይባታለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የቤተሰብ ክትትልና አስተዳደግ ብሎም ለዕድሜዋ ተገቢ ያልሆነ ፊልም ተጽእኖ ይመስለኛል፣ እሷም ራሷ ቲቪ አፍሪካ ላይ ላቪንግ የሚለውን ፊልም በጣም እንደምትወደውና እንደምትከታተለው አልሸሸገችኝም፣ ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ይህቺ ልጅ ይህን ፊልም ባታይ መልካም ነው”
እናትየው ምክሬ ብዙም ቅም አላላቸው፡፡ እንደሚታወቀው እንደ ብዙ ሐብታም ቤተሰብ፣ እዚያም ቤተሰብ ውስጥ አጓጉል ነፃነትና፣ ግዴታ አልባ መብት ያለቅጥ ተንሰራፍቶ ይታይ ነበር፡፡ ልጆቹ እላፊ ሄደው በዕድሜያቸው ያልተገባ ነገር ቢያደርጉ፣ ግሳፄ እንኳ ከስንት አንድ ነው የሚያገኙት እንኳን ቅጣት፡፡
የማታ ማታ ያቺ የደረጃ ተማሪ የነበረች ልጅ አይወርዱ መሽቆልቆል አሽቆልቁላ ከዕለታት አንድ ቀን እናቷ የትምሕርትቤት ሪፖርት ካርዷን ይዘው፣
“ይኼውልህ እንግዲህ ያንተ ውጤት አየኸው?! አንተ እያለህ ልጄ እንዲህ አይነት ውጤት ማምጣት አልነበረባትም” ሲሉኝ፣ የፈራሁትና የጠበቅሁት በመሆኑ ብዙም ሳልደነቅ፣
“አዩ ባለፈው ጊዜ ያስጠነቀኩዎ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት ነበር፤ አሁን ግን የተፈራው ነገር ደርሷል፡፡ ለማንኛውም ግን የችግሩ መንስዔ እኔ ሆኜ በመታየቴ አዝናለሁ፡፡ ምክንያቱም ለልጃችሁ ውጤት መበላሸት ተጠያቂው፣ የእናንተ ቁጥጥር መላላት ነው፣ ልጅቱ እድሜዋ የማይፈቅዱላትን ፊልሞች ስትመለከትና በዚያ ተነድታ ስትወሰድ ዝም ብላችሁ አይታችኋልና” እያልኩ ራሴን ለማስመለጥ የቻልኩትን ያህል ብጥርም፣ ውጤት እንዳልቀናው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ከመባረር አልዳንኩም፡፡
አሁን አሁን አያሌ ወላጆች፣ ልጆች የፈለገ ጥፋትና የማይገባ ነገር ቢያደርጉ፣ ዝንባቸው እሽ “እንዲባል አይፈልጉም፤ በተለይም በዕውቀት በልጽገናል በሐብት ደርጅተናል የሚሉቱ፣ ዳይስፖራ ቀመስ ወላጆች፡፡ ምንድነው ምክንያታችሁ?” ሲባሉ፣ “የልጆቻችንን መብት ላለመንካት ነው” ይላሉ፡፡ ግን ግን የልጅም መብት ማክበር እንዲህ መረን እየለቀቁ ነው እንዴ? . . .
አንድ ጊዜ እንደውም የሰማሁት የአንድ ባለሐብት ልጅ በአባቱ ሽጉጥ እቃ እቃ ሲጫወት እንደ መብት ተቆጥሮለት ታልፏል አሉ፡፡ ሌላ ቤት ደግሞ ልጅ አባዬ ራበኝ ስላለ አፈር ብላ ተብሎ በኩርኩም ቁንጮው የሚላጭ ልጅ የትየለሌ ነው፡፡ ልጅ አግድም አደግ ሆኖ እንዳያድ ግን፣ ገና በብላቴናነቱ በአርጩሜ ሾጥ ቢደረግ፣ ክፋት የለውም፡፡
መልካም ሰብዕና ከመልካም ቤተሰብ እንደሚገኝ ሁሉ፣ መልካም ማኅበረሰብ ደግሞ የመልካም ቤተሰብ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ በስልጣን ወንበሩ ላይ ያሉት መሪዎቻችን ወደድንም ጠላንም የቤተሰብና የማኅበረሰቡ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰው ያልዘራውን አያጭድምና፡፡ መሪን የሚቀርጸው ቤተሰብ ነው፣ ቀጥሎ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ታዲያ መሪዎቻችን ከፉም ለሙም የቤተሰብና የማኅበረሰብ ውጤት በመሆናቸው፣ ቤተሰብ ጋ በደንብ ሊሠራ ይገባል፡፡
ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ።
መጽሐፈ ምሳሌ 19፥18
ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል።
መጽሐፈ ምሳሌ 29፥17

